ምርጫው ይራዘማል ?
ምርጫው ይራዘማል ?
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ስባተኛውን ሀገራዊ የምርጫ ሰሌዳ በሚመለከት የፖለቲካ ፓርቲዎችን ለማወያየት ለጋዜጠኞች ዝግ የሆነ ስብሰባ ትናንት አድርጎ ነበር፣ ይሁንና ፓርቲዎቹ በጊዜ ሰሌዳው ላይ ከመወያየታችን በፊት የሀገሪቱ ሰላምና ፀጥታ ነፃ ምርጫ ለማድረግ አስቻይ አይደለም የሚል መከራከሪያ አቅርበዋል ።
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ሰባተኛው አገር ዓቀፍ ምርጫ የሚካሄድበትን ረቂቅ የጊዜ ሰሌዳ ለፖለቲካ ፓርቲዎች ለውይይት ባቀረበበት ወቅት ተቃውሞ እንደገጠመውም ተሰምቷል። ለጋዜጠኞች ዝግ የነበረው የቦርዱ እና የፖለቲካ ፓርቲዎች ተወካዮች ወይይት ዋና አጀንዳ የምርጫው ማካሄጃ ረቂቅ የጊዜ ሰሌዳ ቢሆንም ፣ የውይይቱ ተሳታፊ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተወካዮች ግን በአገሪቱ ምርጫ ለማካሄድ ከሰላምና ጸጥታ እንዲሁም ከፖለቲካ ምኅዳር ጋር የተያያዙ አስቻይ ሁኔታዎች በመኖር አለመኖራቸው ላይ ቦርዱ እና ፓርቲዎች ከስምምነት ላይ ባልደረሱበት ሁኔታ በምርጫ ማካሄጃ የጊዜ ሰሌዳ ላይ መነጋገር አንችልም በሚል ተቃውሞ አሰምተዋል ።
የፖለቲካ ፓርቲዎቹ ተወካዮች ግን ኢትዮጵያ ከሰላምና ጸጥታ አንጻር አሁን ባለችበት ነባራዊ ሁኔታ ነጻ እና ፍትሃዊ አገር ዓቀፍ ምርጫ ማካሄድ የሚያስችላት ቁመና ላይ አይደለችም በማለት የምርጫ ቦርድ አመራሮችን እንደሞገቱ ከምንጮች ተረድተናል። አብዛኞቹ ፓርቲዎች በተለይ በአማራ፣ ኦሮሚያና ትግራይ ክልሎች ያሉት የጸጥታ ሁኔታዎች ነጻ እና አሳታፊ ምርጫ ለማካሄድ አስቻይ አይደሉም የሚል አቋም ይዘው ከስብሰባው ተበትነዋል ተብሏል ።